የተማሪ ኬር ዲጂታል ጤና አገልግሎት ምን አዲስ ነገር ይዟል?
በኢትዮጵያ በብዙ ሺዎች የሚገመቱ ተማሪዎች በየዓመቱ ከየከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ቢመረቁም፣ ስራ ማግኘት ግን ፈተና እየሆነ መጥቷል። አንዳንዶች የመንግስት ስራ ሲጠብቁ ቢስተዋልም፣ ሌሎች ደግሞ በራሳቸው ስራ ወደ መፍጠር እየገቡ ይገኛሉ። ለእዚህም ነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ቁጥራቸው ይነስ እንጂ ተመራቂዎች ከስራ ጠባቂነት በመውጣት በራሳቸው ስራ ፈጣሪ ሆነው የስራውን ዓለም ሲቀላቀሉ የሚታየው። እነዚህ ምሩቃን በተማሩት የሙያ መስክ አዲስ ሀሳብ በማፍለቅ ስራ እየፈጠሩ ይገኛሉ፤ በእዚህ የፈጠራ ሀሳባቸው አዳዲስ ስራዎችን በመጀመር ከራሳቸውም አልፈው ለሌሎችም ሲተርፉ ይስተዋላሉ።
ዶክተር ኪሩቤል ጫንያለውና ሦስት የሙያ አጋሮቹም ከእነዚህ መካክል ይጠቀሳሉ። የቡድኑ አባላት በሕክምና ትምህርት ከተመረቁ በኋላ ወደ ሥራ ዓለም ለመግባት ተቀጥረው ለመስራት ፍላጎቱ ያላቸው ቢሆንም፣ ወቅቱ መንግሥት የሕክምና ባለሙያዎችን ወደ ስራ መመደብ ያቆመበት ስለነበር ሥራ ሳያገኙ ይቀራሉ። የሥራ ልምድ የሌላቸው መሆናቸው ደግሞ በራሳቸው ተሯሩጠው ሥራ ማግኘት የሚችሉበትን ጥረትም የሰማይ ያህል ያርቅባቸዋል። ይህን ጊዜ ተመራቂዎቹ አብረው መምከር ይጀምራሉ። በተማሩበት የሕክምና ትምህርት አዳዲስ መንገዶችን በመከተል ሀሳብ በማፍለቅ ‹‹አይ ጤና (i- Tena)›› የተሰኘ ዲጂታል ሜዲካል ላይ ያተኮረ ፕላትፎርም መሰረቱ።
በአይ ጤና (i- Tena ) ሀረግ ውስጥ ትንሿ የላቲን ፊደል ‹‹አይ›› በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትወክለው ኢኖቬሽን፣ ኢንተርኔት እና የመሳሰሉትን ሀሳቦች ነው። እነርሱም ኢኖቬሽን የሚለውን መርጠው በመውሰድ ‹ኢኖቬሽን ጤና› በማለት በጤና ላይ ያሉ ክፍተቶችን በመለየት አዳዲስና ያልተለመዱ ሥራዎችን ለመስራት አቀዱ፤ ከዚያም አይ ጤና (i- Tena) ዲጂታል ሜዲሲን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርን መስርተው ሥራቸው ‹አሃዱ› አሉ።
የስራ ፈጠራ ሀሳባቸውን በተመለከተ የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገረው የአይ ጤና (i- Tena) እና ተማሪ ኬር (Temari care) መስራችና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ኪሩቤል ጫንያለው እንደተናገረው፤ ድርጅቱ በየተቋማቱ በሚሰጡ የጤና እንክብካቤ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል። ከተመሠረተ አምስት ዓመታትን አስቆጥሯል።
ድርጅቱ ሥራውን የጀመረው የጥሪ ማዕከል በመክፈት ቴሌ ሜዲሲን የተሰኘ አገልግሎት በመስጠት ነው፤ በዚህም ለሁለት ዓመታት ያህል ሰርቷል። በዚህ ሥራ ላይ ሳለ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ሁሉም ነገሮች ወደ ዲጂታል ሲለወጡ የተመለከቱት እነ ዶክተር ኪሩቤል፣ ከወቅቱ ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል ሀሳብ ማምጣት እንዳለባቸው ያምናሉ፤ የተደራጀ የጤና ሥርዓት ክፍተት መኖሩንም ይረዳሉ። አዲስ ሀሳብ በማምጣት በተለይ በትምህርት ቤቶች የተደራጀ የጤና አገልግሎት ማቅረብ የሚያስችል ሀሳብ ያመነጫሉ።
ይህን ሀሳባቸውን መሰረት በማድረግም ተቋምን መሠረት ያደረገ የጤና አጠባበቅ (Institution Based Helth Care) አገልግሎት በሚል አዲስ የፈጠራ ሀሳብ ያመነጫሉ። በዚህ ሀሳባቸውም እኤአ በ2020 የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ባዘጋጀው ሀገር አቀፍ ብሩህ ተስፋ ውድድር ላይ ቀርበው ሁለተኛ መውጣት ችለዋል።
የተደራጀ የጤና አገልግሎት መስጠት ሲባል ሕክምና ብቻ መስጠት ሳይሆን ጤና መከላከል፣ ጤናን ማስተዋወቅ፣ የምርመራ አገልግሎትና ሁሉንም በአንድነት በተቀናጀ መልኩ መስጠት የሚያስችል እንደሆነ ዶክተር ኪሩቤል ያብራራል። በተለይ እንደ ሀገር አብዛኛውን ጊዜ የተለመደው የምርመራና ሕክምና አገልግሎት መስጠት መሆኑን ይናገራል።
የተለመደው አካሄድ አንድ ሰው ሲያመው ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ያለበትን ሕመም ተናግሮ ሕክምና ተሰጥቶት ወደ ቤት መመለስ ነው እንጂ መከላከል እና ጤናን ማስተዋወቅን ማእከል ያደረገ አይደለም ሲል ገልጾ፣ አዲሱ የተቀናጀ የሕክምና አገልግሎትም በየትምህርት ቤት ውስጥ ሀኪም አስገብቶ ማከሙ አንድ ነገር ሆኖ መከላከልና ጤና ማስተዋወቅ ላይም በሰፊው ለመስራት በማሰብ መሆኑን ይገልጻል።
ዶክተር ኪሩቤል እንደሚለው፤ ይህ ‹‹ተማሪ ኬር›› የተሰኘ የጤና አገልግሎት የተደራጀ የምርመራና መከላከል ፕሮቶኮሎችም አሉት። በአገልግሎቱ ከአምስት እስከ ስድስት የሚሆኑ ዓመታዊ ምርመራዎች በስፔሻሊስት ሀኪሞች ይሰጣሉ። ለአብነት የአይን፣ የጥርስ፣ የአመጋገብ ሥርዓት፣ ቆዳ እና መሰል ሕመሞች ምርመራ ይደረጋል።
‹‹እኛ በምንሰራባቸው ትምህርት ቤቶች ከሚመሩ ተማሪዎች 10 በመቶ ያህል የሚሆኑት የአይን ሁኔታቸው በጣም አስቸጋሪ ነበር። አይን ደግሞ ትምህርትን በትክክል ለመቀበል ወሳኝ ነው፤ በመሆኑም እንደዚህ አይነቶቹ የጤና ችግሮች ላይ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው›› ሲል አብራርቷል።
ዶክተር ኪሩቤል እንደሚናገረው፤ በጤና ማስተዋወቅም እንዲሁ የተማሪዎቹን እድሜና የትምህርት ደረጃ ያማከለ የሕክምና ትምህርት ይሰጣል፤ ጎን ለጎንም የትምህርት ቤት ማህበረሰቡንና ወላጆችን ጭምር በጤና ዙሪያ ለማብቃት የሚረዳ ጤናን የማስተዋወቅና ስልጠና ይሰጣል። ፍላጎቱ ላላቸው የትምህርት ቤቱ ማህበረሰቦችና ወላጆች በወር አንድ ጊዜ በተለያዩ ርዕስ ጉዳዮች ዙሪያ የጤና ስልጠና በመስጠት በጤና ጉዳይ ብቁ እንዲሆኑ አድርጎ ሰርተፊኬት እንደሚሰጥም ይገልጸል።
እንደ ዶክተሩ ማብራሪያ፤ ዓመታዊ የጤና ፌስቲቫል በትምህርት ቤቶች ይዘጋጃል፤ ይህ ደግሞ የጤና ባህልን ለማዳበር ይረዳል፤ አብዛኛዎቹን በሽታዎች መከላከል የሚቻል ሆኖ ሳለ አስቀድሞ የመመርመር ባህሉ ስላልዳበረ ሁሉ ጊዜ ችግር ከተፈጠረና በሽታ ከተባባሰ በኋላ ነው ወደ ሕክምና የሚገባው። በዚህ የጤና ፌስቲቫል ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር አይናቸውን፣ ጥርሳቸውን፣ ቆዳቸውንና ሁሉንም የጤንነት ሁኔታቸውን ለማወቅ ምርመራ ይደረግላቸዋል፤ በላብራቶሪ ታይቶ እና የባለሙያ ምክር አግኝተው ያሉበትን የጤና ሁኔታ እንዲያውቁ ይደረጋል። በሀኪም ቀጠሮ በቋሚነት ለተማሪዎች ምርመራና የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥበት አሠራር እነ ዶክተር ኪሩቤል ፈጥረዋል።
አይ ጤና (i- Tena) እና ተማሪ ኬር (Temari care)ፕላትፎርም በዌብ ሳይት የተለያዩ የጤና አገልግሎቶች እየሰጠ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት 11 ትምህርት ቤቶች በተማሪ ኬር አገልግሎቶች ተጠቃሚ ሆነዋል። ተማሪ ኬር በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ክሊኒክ በመክፈት 17 የሚሆኑ ሀኪሞች በቋሚነት ቀጥሮ አገልግሎት እንዲሰጥ እያደረገ ነው። ከእነዚህ መካከል በየቀኑ ክትትል ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ ስቴሻሊስት ሀኪሞችም አሉት።
ዶክተር ኪሩቤል እንዳብራሩት፤ የተማሪ ኬር አገልግሎት በትምህርት ቤቱ ማህበረሰብና በወላጆች ፍላጎት ላይ ተመስርቶ ነው የሚሰጠው። ተማሪዎቹም ለሚሰጣቸው አገልግሎት ወርሃዊ ክፍያዎችን ይፈጽማሉ። ክፍያው በተማሪዎች ብዛት የሚወሰን ሲሆን፣ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ተማሪዎች ቁጥር ሲጨምር ክፍያው ይቀንሳል፤ የተማሪ ቁጥር ካነሰ ደግሞ በዚያው ልክ ክፍያው ይጨምራል፤ ያም ሆኖ ግን እስካሁን የአንድ ተማሪ ወርሃዊ ክፍያ ከ100 እስከ 300 ብር ነው። የስልጠና፣ የተማሪና ወላጅ ምርመራው እና ፌስቲቫል አገልግሎት ክፍያ በየወሩ በሚደረገው ክፍያ የሚሰጥ ነው። ተማሪዎች ይህን ክፍያ ሳይፈጽሙ ሁል ጊዜ የራሳቸውና የቤተሰባቸው ሀኪም አላቸው ማለት ነው።
የተማሪው የሕክምና መረጃ /ዳታ/ ሜዲካል ሪከርድስ በትክክል ተይዞ ለወላጆች ሪፖርት ይደረጋል። ድርጅቱ ከላብራቶሪ፣ ስፔሻሊቲ ማዕከላት እና ሆስፒታሎች በአጠቃላይ ከ47 በላይ ድርጅቶች ጋር አብሮ እየሰራ ይገኛል። ተማሪዎቹ ያለባቸው የሕመም አይነት ከፍተኛ ሆኖ ሆስፒታል ደረጃ መታከም ካለባቸው በቀጥታ ወደ ሆስፒታል ሪፈር የሚደረጉበት አሰራርም አለው። ሆስፒታሎች በፍጥነት እንዲቀበሏቸውና በቅናሽ ዋጋ እንዲያክሟቸው የሚያስችል ምቹ ሁኔታ የተፈጠረበትም ነው።
በጤና አገልግሎቱ በትምህርት ቤቶች ማንኛቸውም አይነት የሕክምና አይነቶች ይሰጣሉ፤ ከዚህ ባሻገር ቋሚ የሚባሉ በሽታዎች የሚባሉት እንደ ስኳር፣ የሚጥል በሽታና የመሳሰሉት ላለባቸው ተማሪዎች ደግሞ ቋሚ ክትትል ይደረግላቸዋል። ትምህርት በሌለባቸው ቀናትም ተማሪው ላይ የሕመም ምልክቶች ከታዩ ወላጆች ከሀኪሙ ጋር መነጋገር የሚችሉበት ሁኔታ ተመቻችቷል።
‹‹ተማሪ ኬር አንድ ተማሪ ለሕክምና በዓመት ሊያወጣ ከሚችለው ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆነውን ወጪ የሚቀንስ አገልግሎት እየሰጠ ነው›› ሲል ዶክተር ኪሩቤል ይገልጻል። በአገልግሎቱ አንድ ተማሪ የራሱ ሀኪም እንዲኖረው እንደሚደረግ ጠቅሶ፣ በዚህም ተማሪው ያለበት የሕመም አይነት በሚገባ ስለሚታወቅና ክትትል ስለሚደረግለትም ወላጆች ለረባው ላረባው ሕክምና የሚያወጡትን የሕክምና ወጪ ያስቀራል ብሏል። ለተማሪዎች በየጊዜው የሕክምና ክትትል መሰጠቱ ከሁሉም በላይ የተደበቁ ሕመሞችን ለማግኘት ማስቻሉንም አስታውቆ፣ በድንገት የሚከሰቱ እስከ ቀዶ ሕክምና የሚያደርሱ እንደ የአይንና የመሳሰሉት ብዙ አይነት ሕመሞች መገኘታቸውን አመልክተዋል።
ከሁሉም በላይ የቅድመ ምርመራ ባህልና ጤና የማስተዋወቅ ሥራዎች ሲሰሩ ልጆችን መሰረት አድርጎ በመሆኑ ለጤና እድገት ጠቃሚ ነው። የሌሎች አገራትን ተሞክሮ ዋቢ አድርጎ ሲያብራራም፣ ሀገሮቹ የጤና እድገት ያሳዩት ትምህርት ቤት ላይ መሠረት አድርገው በመስራታቸው ነው ብሏል። ይህን አገልግሎት ልጆች ከልጅነታቸው ጀምሮ ቀድሞ የመመርመር ባህልን እንዲያዳብሩና እየተማሩ እንዲያሳድጉ ለማድረግ ይረዳል ሲል ገልጧል።
የዩኒሴፍን መረጃ ዋቢ አድርጎ ዶክተር ኪሩቤል፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ 48 በመቶ የሚሆነው እድሜው ከ18 ዓመት በታች ነው ሲል ገልጿል። እሱ እንዳለው፤ ይህ ደግሞ በጣም ትልቅ የወጣት ነው። ለእዚህ ወጣት አሁን በትክክል ስለጤና ማሳወቅ ያስፈልጋል። ይህ ስራ ከተለመደው የጤና አገልግሎት አልፈን በመሄድ ብዙዎች ስለጤናቸው ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸው ለማድረግ፣ ቤተሰባቸውን መንከባከብ የሚችሉ ዜጎችን ለመፍጠር ያስችላል።
በተማሪ ኬር አገልግሎት ከተማሪዎች ባሻገር አገልግሎቱ ካገኙት ወላጆች መካከል ብዙዎቹ የተለያዩ ሕመሞች ተገኝቶባቸዋል። ተማሪዎችም እንዲሁ በስልክና በመሰል አሌክትሮኒክስ ነገሮች ላይ አብዛኛውን ጊዜያቸው የሚያሳልፉ እንደመሆናቸው ለተለያዩ የጤና ጉዳቶች እየተጋለጡ ይገኛሉ። በጤና ትምህርቱ ተማሪዎች እንዲሳተፉ በማድረግ ለህጻናቱ በመዝሙር፣ ለትላልቆቹ ደግሞ የተለያዩ ስልጠናዎች በመስጠት እንዲበቁ የሚያደርጉ ስራዎች ይሰራሉ።
‹‹በሚያገኙት አገልግሎት ተማሪዎች ሆኑ ወላጆች በጣም ደስተኛ መሆናቸው ባገኙት አጋጣሚዎች ይገልጹልናል ሲል ተናግሯል። ‹‹ለትምህርት ቤቶችም ከባድ የራስ ምታት ነው ያቀለልንላቸው ምክንያቱም አብዛኛው ተማሪ ተጋጭቶና ወድቆ ወደ ሕክምና ሲመጣ ይዘው የሚመጡት አስተማሪዎችንና ዳይሬክተሮችን ነው። የኛ በአካባቢው መገኘት አስተማሪ ትምህርቱ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ ያስችላል፤ የተማሪውን ጤና በተመለከተ ደግሞ እኛ እየሰራን ተጋግዘን ተማሪዎችም በትምህርት ላይ ትኩረታቸው እንዲጨምርና ውጤታማ እንዲሆኑ ያስችላል። ›› ሲል አብራርቷል።
ተማሪ ኬር ለትምህርት ቤት ማህበረሰቡም እንዲሁ ሕክምና በነጻ ይሰጣል የሚለው ዶክተር ኪሩቤል፤ ተማሪው፣ ወላጁ እና የትምህርት ቤት ማህበረሰቡ በአጠቃላይ ሁሉም የየራሳቸው ሀኪም አላቸው እንደ ማለት ነው ሲል ያብራራል። በአጠቃላይ በአገሪቱ ያለው የሀኪም ተደራሽነት 53 በመቶ ያህል ብቻ መሆኑን ጠቅሶ፣ ያንን ቁጥር በማሳደግ በየትምህርት ቤቱ የጤና አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ ላይ እንደሚሰራም ተናግሯል፤ በየትምህርት ቤቱ ምገባ ተብሎ እንደሚሰጠው ሁሉ የእነሱ የጤና አገልግሎትም ወደ ትምህርት ቤቶች እንዲገባና ውጤት አሳይቶ ተደራሽነቱ እንዲቀጥል ዓላማ ተደርጎ እንዲሚሰራም ይናገራል።
በተለይ የጤና ፊስቲቫሉ የጤና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትንና የሕክምና ባለሙያዎችን ከህብረተሰቡ ጋር ለማገናኘት ያለመ ነው የሚለው ዶክተር ኪሩቤል፤ በአንድ ሁነት ከ15 በላይ ድርጅቶችን በማሳተፍ የቆዳን፣ የአይን፣ የጥርስ፣ የአንገት በላይ፣ የስነ ምግብ፣ የሥነ አእምሮ፣ ሆስፒታሎች፣ ላብራቶሪዎች ሁሉ በእዚህ እንዲሳተፉ ይደረጋል ብሏል። ይህም ተቋማቱ ራሳቸውን ከሕብረሰተቡ ጋር እንዲያገናኙና ሕብረተሰቡም የሚፈልገውን አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ እንደሚያስችልም ጠቁሟል።
የጤና ፌስቲቫሉ ተገልጋዮች አገልግሎቱ ጥሩ መሆኑን እንደሚገልጹም አስታውቋል፤ አብዛኛው ሰው የመመርመር ባህሉ ደካማ መሆኑን ተናግሮ ‹‹ሳይታመም አይኑን፣ ቆዳውንና የመሳሰሉትን የሚመረመርና የሕክምና ሁኔታውን የሚከታተል ምን ያህሉ ነው›› የሚለው ቢታይ ምላሹን ለመገመት ይከብዳል ሲል ጠቅሶ፣ ‹‹ልጆቹ ሕክምና ላደርግ ነው ምን ይገጥመኝ ይሆን›› የሚለው ፍራቻ ሳይኖርባቸው በሚያወቁት አካባቢ ላይ የጤና ሁኔታቸውን ማወቃቸው ደስተኛ እንዲሆኑ እንደሚያደርጋቸው ይገልጻል። ከሀኪሞቻቸው ጋር በግልጽ እንዲነጋገሩ እንዲሁም ሳያውቁት ጤናቸውን እንዲጠብቁና የጤና ክትትል እንዲያደርጉ የሚረዳ ትልቅ አገልግሎት መሆኑን ተናግሯል።
እሱ እንዳብራራው፤ እነ ዶክተር ኪሩቤል ስራውን አራት ሆነው ቢጀምሩም፣ በአሁኑ ወቅት ሁለቱ በተለያየ ምክንያት ከሀገር ውጭ ናቸው። የተቀሩት ሁለቱ ሥራውን ቀጥለዋል። ድርጅቱ አሁን 20 ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ እድል በመፍጠር በቋሚነት ቀጥሮ እያሰራ ይገኛል። ወደፊት ተደራሽነቱን እያሰፋ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጠራል።
ይዘው የተነሱትን ሀሳብ በየጊዜው በማሻሻልና በማስተካከል ትምህርት ቤት ላይ ትኩረት አድርገው በመስራት በአካልም ሆነ ዲጂታል በሆነ መልኩ በጤና ላይ አተኩረው እየሰሩ ናቸው። በቀጣይም ትላልቅ ፕሮጀክቶችን የመስራት ሀሳቡ አላቸው። የጤና ተደራሽነትን ለማስፋት የተለያዩ ተቋማትን መሰረት ያደረጉ ልክ እንደ ተማሪ ኬር አይነት ተመሳሳይ የተቀናጀ የጤና አገልግሎት ስራዎችን ሕብረተሰቡ ባለበት ቦታ ዘልቆ በመግባት ተደራሽነትን ለማስፋት እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም ይገልጻል።
አሁን ላይ መንግሥት በተለይ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችን የሚያበረታቱ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን አመልክቶ፣ ይህ ድጋፍ ግን በተግባር እንዲገለጽም ጠይቋል። በተለይ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በኩል ያለው ድጋፍ የላለ መሆኑን ጠቁሞ፣ ‹‹ለምሳሌ እኔ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በፈጠራ ሥራ ድጋፍ አድርጎልኛል፤ የጤና ሚኒስቴር ግን እውቅና ለመስጠት ረጅም ጊዜ ወስዶበታል። ጤናና ትምህርት ላይ እየሰራሁ እንዴት ትምህርት ሚኒስቴር እውቅና መስጠት ያቅተዋል›› ሲልም አመልክቷል። እንደዚህ አይነት ችግሮች ጎታች መሆናቸውን አስታውቆ፣ ስራው ጠቀሜታ ያለውና የሥራ እድልም የሚፈጥር መሆኑ ከታመነበት ስራ ላይ እንዲውል ለማድረግ አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ በፍጥነት ሊደረግ እንደሚገባ አስገንዝቧል።
ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ሀሳባቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያደርጉት ጉዞ አልጋ በአልጋ እንዳልሆነና ከሚጠበቁት በላይ ከባድ ሊሆን እንደሚችል አስታውቋል። ይህንንም አስቀድመው ሊረዱት እንደሚገባም አመልክቶ፣ ይህን አውቀው ወደ ስራው ከገቡና የያዙት ሀሳብ የሚያምኑበት ከሆነ ጥረትና ትግላቸውን እስከ መጨረሻ መቀጠል እንዳለባቸውም አስገንዝቧል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም